ህጋዊ እና ህገ-ወጥ የሥራ ውል መታገድ ውጤት


የሥራ ውል መታገድ

የህጋዊ ዕገዳ ውጤት

በህጉ ላይ በተዘረዘሩት አጥጋቢ ምክንያቶች የተነሳ ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች ለጊዜው መታገድ የሠራተኛውን የመስራት ግዴታ እና የአሠሪውን ደመወዝ የመክፈል ግዴታ ለጊዜው ቀሪ ያደርጋል። ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው ዕገዳ የሥራ ውሉን ለጊዜው የማቋረጥ ሆነ ቀሪ የማድረግ ውጤት ስለሌለው የአገልግሎት ዘመን አይቋረጥም። ስለሆነም የስንብት ክፍያ ለማስላት፣ የማስጠንቀቂያ ጊዜን ለመወሰን እንዲሁም የሥራ ልምድ የምስክር ወረቀት ለመስጠት ዕገዳው ጸንቶ የነበረበት ጊዜ ከሠራተኛው የአገልግሎት ዓመት ላይ ተቀናሽ ሊደረግ አይገባውም።

የዕገዳ ጊዜ ማብቃት

የዕገዳው ጊዜ ሲያበቃ ውጤቱም አብሮ ያበቃል። ማብቃቱን ተከትሎ ሠራተኛው በሚቀጥለው ቀን በሥራ ቦታው ላይ መገኘት አለበት። በአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 22 የዕገዳ ጊዜው ሲያበቃ የአሠሪው ግዴታ ሠራተኛውን ወደ ሥራው እንዲመልሰው ግዴታ ጥሎበት ነበር።[1] ይህ አንቀጽ በአዋጅ ቁ. 1156/2011 ተሻሽሏል። በማሻሻያው መሰረት አሠሪው ሠራተኛውን የሚመልሰው ወደ ቀድሞ ሥራው ሳይሆን ሲከፈለው የነበረውን ደመወዙን በመጠበቅ ከሙያው ጋር አግባብነት ባለው የሥራ መደብ ላይ ነው። ይህ ለምን አስፈለገ? የአዋጁ ሐተታ ዘምክንያት እንደሚነግረን ማሻሻያው ያስፈለገበት ምክንያት የእገዳ ጊዜ ማብቃት ተከትሎ ሠራተኞች ወደ ስራ ሲመለሱ ከምደባ ጋር ተያይዞ እየተነሱ ያሉ የስራ ክርክሮች መፍትሄ ለመስጠት እንዲቻል ነው።

የዕገዳ እርምጃ መነሻ ምክንያት የድርጅቱን ሥራ በከፊል የሚቀንስ ወይም በሙሉ የሚያስቆም ያልተጠበቀና ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ነው። ሠራተኛው ሲታገድ የሥራ መደቡም ክፍት ሆኖ ይቆያል። የዕገዳ ጊዜው ሲያበቃ ሠራተኛው ክፍት ሆኖ በሚቆየው የሥራ መደቡ ላይ ይመለሳል። ስለሆነም ዕገዳ በባህርዩ ከምደባ ጋር ተያይዞ የሚያስነሳው የሥራ ክርክር የለም። ክርክር ሊነሳ የሚችለው በታገዱት ሠራተኞች የሥራ መደብ ላይ አሠሪው ሌሎች ሠራተኞች የቀጠረ እንደሆነ ነው። ይህ ደግሞ ዓይን ያወጣ ህገ-ወጥነት ነው። ድርጅቱ ሌሎች ሠራተኞችን የሚያስቀጥር ሥራ ከነበረው ከመሻው የዕገዳ እርምጃ የተወሰደው ለዕገዳ የሚያበቃ እውነተኛና ተጨባጭ ምክንያት ባልነበረበት ሁኔታ እንደሆነ ያሳያል። ማሻሻያው በዕገዳ ስም የሚደረግን ህገ-ወጥ የምደባ ለውጥ ከመከላከል ይልቅ ህገ-ወጥነትን ያበረታታል።

የዕገዳ ምክንያት አለማብቃት

የዕገዳ ጊዜ ማብቃት የዕገዳ ምክንያት ማብቃትን አያሳይም። አሠሪውን የሚመለከቱ የማገድ ምክንያቶች አሠሪው ከተፈቀደለት ወይም በህጉ ከተቀመጠው የዘጠና ቀናት ጊዜ በላይ ሊዘልቁ ይችላሉ። ይህ ሲሆን የአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 21(2) ሠራተኛውን የስንብት ክፍያ እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ የማግኘት መብቱን ይጠብቅለታል። ክፍያዎቹ የሥራ ውል መቋረጥ ውጤቶች እንደመሆናቸው ውሉ የሚቋረጥበት መንገድ ሳይታወቅ ስለክፍያ ማውራት ከማደናገር የዘለለ ፋይዳ የለውም። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚወስነው ወይም በህጉ ከተቀመጠው የዘጠና ቀናት ማብቃት በኋላ የዕገዳ ምክንያት አለማብቃት (መቀጠል) በራሱ የሥራ ውልን የሚያቋርጥ በቂ ምክንያት አይደለም። ይህ ፈጦ የወጣ የህጉ ግድፈት በማሻሻያው መስተካከል ቢኖርበትም ከመስተካከል ይልቅ ችግሩ ገዝፎ እንዲባባስ ተደርጓል።

አዋጅ ቁ. 1156/2011 በአንቀጽ 21(2) ላይ ‘ካመነ’ ከሚለው ቀጥሎ ‘ሠራተኛው የቅጥር ውሉ ተቋርጦ’ የሚል ሐረግ ጨምሮበታል። ‘ካመነ’ በሚል ልኩ የማይታወቅ ተለጣጭ ስልጣን (discretion) የሚያጎናጽፈው ማሻሻያ ስልጣኑ የተሰጠው አካል ይህን ስልጣን በመገልገል ስለሚሰወደው እርምጃ ወይም ውሳኔ በዝምታ አልፎታል። ‘ሠራተኛው በአንቀጽ 39 እና 44 የተመለከቱትን ጥቅሞች የማግኘት መብት አለው።’ የሚለው የቀድሞው አዋጅ ሆነ ‘ሠራተኛው የቅጥር ውሉ ተቋርጦ በአንቀጽ 39 እና 44 የተመለከቱትን ጥቅሞች የማግኘት መብት አለው።’ የሚለው አዲሱ አዋጅ ሁለቱም በውሉ ዕጣ ፈንታ ላይ ማን ወሳኝ እንደሚሆን ግልጽ አላደረጉትም። ውሉ የሚቋረጠው በህግ በተደነገገው መንገድ? በሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ባለው ባለስልጣን ውሳኔ? ወይስ በአሠሪው አነሳሽነት?

ከሥራ ውል የሚመነጭ መብትና ግዴታ ለጊዜው መታገድና የዕገዳው ምክንያት አለማብቃት በቀጥታ ወደ ሥራ ውል መቋረጥ ያመራበት ምክንያት ሐተታ ዘምክንያቱ ሊመልሰው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ አሠሪው ሥራውን እንደገና ለመቀጠል የማይችል ከሆነ በአንድ ተቋም ዕምነት ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ ሊረጋገጥ ይገባል። ማረጋገጫ ከተገኘ ደግሞ የሥራ ውሉ ሊቋረጥ የሚችለው በአንቀጽ 24/4/ (ድርጅቱ በመዘጋቱ) ወይም በአሠሪው አነሳሽነት በአንቀጽ 28(2) ሀ (በቅነሳ) ነው። ዕገዳ መኖሩ የሁለቱን ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት ሊያስቀር እንደማይገባ ግልጽ ነው። 

የዕገዳ ጊዜ ማብቃትን ተከትሎ አሠሪው ምን ማድረግ አለበት? ወይም ውሉን በየትኛው ድንጋጌ መሰረት ማቋረጥ አለበት? የሚለው ጥያቄ ሊያስጨንቅ የሚገባው አሠሪውን እንጂ አስፈጻሚውን አካል አይደለም። ለዕገዳው ምክንያት የሆነው ነገር ከዕገዳ ጊዜው በላይ ቢቀጥልም ባይቀጥልም የዕገዳ ምክንያት አለማብቃት ህጋዊ ውጤቱ በአንቀጽ 22 ላይ ከተቀመጠው ውጪ አይወጣም። የዕገዳ ጊዜው እስካበቃ ድረስ የዕገዳው ምክንያት አበቃም አላበቃም ለጊዜው ታግደው የነበሩት መብትና ግዴታዎች ውጤት ማግኘት ይጀምራሉ። ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ‘ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ካመነ’ የሚወስነው አይደለም። ከዚያ ይልቅ ከዕገዳው ማብቃት በኋላ ከአቅም በላይ የሆነው ምክንያት ወይም ያልታሰበ የገንዘብ ችግር ካልተወገደ የመዋቅር ለውጥ ማድረግ፣ የቅነሳ እርምጃ መውሰድ፣ ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ብሎም መፍትሔ ሊሆን የሚችል የተለየ ዕቅድ መቀየስና መተግበር በአጠቃላይ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት አይቶ ይበጀኛል የሚለውን መወሰን የአሠሪው ስልጣን ነው።

የህገ-ወጥ ዕገዳ ውጤት

ሠራተኛውን በሚመለከቱ ምክንያቶች የዕገዳው ምክንያት መኖር እንጂ ህጋዊነቱ ጥያቄ ሆኖ አይነሳም። በአንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 4 በተመለከቱት ምክንያቶች ሠራተኛው ከሥራ ሲቀር በአሠሪው ከሚወሰድበት የስንብት እርምጃ ከለላ ያገኛል። በተጨማሪም ሥራውን በገዛ ፈቃዱ እንደለቀቀ ግምት እንዳይወሰድበት እነዚህን ምክንያቶች እንደ መከላከያ ሊያቀርባቸው ይችላል። ለመሆኑ ከሥራ ለመቅረቱ በቂ የዕገዳ ምክንያት እንደነበረው ማስረዳት የሚችለው እንዴት ነው?

በአንቀጽ 18(1) እና (2) ፈቃድ እንደተሰጠ መረጋገጥ ያለበት ሲሆን በንዑስ አንቀጽ 3 ደግሞ ሠራተኛው ታስሮ እንደነበረና የታሰረበት ጊዜም ከ30 ቀናት እንደማይበልጥ እንዲሁም መታሰሩ ለአሠሪው እንደተነገረው ወይም የሚያውቅበት መንገድ ስለመኖሩ መረጋገጥ ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ብሔራዊ ጥሪን አስታኮ መከላከያ ለማቅረብ ከሥራ መቅረት በብሔራዊ ጥሪ ሳቢያ እንደተከሰተ ሊረጋገጥ ይገባል። ብሔራዊ ጥሪ የፍሬ ነገርና የሕግ ጉዳይ እንደመሆኑ ሠራተኛው የት እንደነበረ በማስረጃ ማረጋገጡ ብቻውን አይበቃም። በፍሬ ነገር የተረጋገጠው ምክንያት የብሔራዊ ጥሪን ትርጓሜ አሟልቶ መገኘት ይኖርበታል። እንበልና አንድ ሠራተኛ በጎርፍ ለተጠቁ ወገኖች እገዛ ለማድረግ በመሄዱ ለአንድ ወር ያህል ከሥራ ቀርቷል። የጎርፍ አደጋ መድረሱና ሠራተኛው አደጋው ቦታ ተገኝቶ አንድ ወር ሙሉ እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱ በማስረጃ ከተረጋገጠ በኋላ ፍሬ ነገሩ ከብሔራዊ ጥሪ ትርጓሜ አንጻር ይመዘናል።

ብሔራዊ ጥሪ የሚለው ቃል ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በመንግስት ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ ጥቅም ላይ ሲውል አይታይም። ከዚህ አንጸር የቃሉን ትክክለኛ ይዘትና ወሰን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ያስቸግራል። ሆኖም ቃሉ አገራዊና ይፋዊ መልክ የያዘ በመሆኑ ብሔራዊ ጥሪ ሲባል አገራዊ ችግር ሲከሰት ዜጎች መንግስት ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት የበኩላቸውን እገዛ የሚያደርጉበት ክስተት ነው ማለት እንችላለን። ወሳኙ ነጥብ የተከሰተው ችግር ስፋትና ጥልቀት ሳይሆን በመንግስት በኩል ይፋዊ ጥሪ መኖሩ ነው። ስለሆነም በአንድ አካባቢ ላይ የጎርፍ አደጋ በመድረሱ ምክንያት እገዛ ለማድረግ በሚል ከሥራ መቅረት ብቻውን በብሔራዊ ጥሪ ውስጥ የሚወድቅ ምክንያት አይሆንም።

በአንቀጽ 18 ከንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 4 የተመለከቱት በቂ ምክንያቶች ሳይኖሩ ሠራተኛው ከሥራ ከቀረ ካለበቂ ምክንያት ክሥራ እንደቀረ ስለሚቆጠር አሠሪው የሥራ ውሉን በአንቀጽ 27/1/ ለ በህጋዊ መንገድ ሊያቋርጠው ይችላል።

አሠሪውን በሚመለከቱ ምክንያቶች ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች ለጊዜው መታገድ መሰረታዊ የሆነውን የሠራተኛውን የመስራት እና ደመወዝ የማግኘት መብት አደጋ ውስጥ ይከታል። ሆኖም መታገዱን በመከልከል አደጋውን ማስቀረት አይቻልም። እንዲያውም እገዳ አስፈሪው የሠራተኞች ቅነሳ እንዳይኖር ተመራጭ መፍትሔ ነው። ህጉ እገዳን ማስቆም ባይችልም የስነ-ስርዓት ቅድመ ሁኔታዎችን በመዘርጋት ለሠራተኛው ጥበቃ ያደርጋል። ጥበቃው ከቅነሳ ጋር ሲነጻጸር ይበልጥ ጠንካራ ነው።

የቅነሳ እርምጃ ሲወሰድ ህጋዊ በቂ ምክንያቶች መኖራቸው የመወሰን ስልጣን ሙሉ በሙሉ ለአሠሪው የተተወ ነው። በተቃራኒው በአንቀጽ 18/1/ እና /2/ መሰረት የዕገዳ እርምጃ ሲወሰድ በድንጋጌዎቹ የተመለከቱት በቂ ምክንያቶች መኖራቸው የሚረጋገጠው በራሱ በአሠሪው ሳይሆን በሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ባለው ባለስልጣን ነው። አሠሪው የዕገዳ እርምጃ ሲወስድ የዕገዳውን ምክንያት ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ላለው ባለስልጣን ካላስታወቀና ዕግዱ ካልፀደቀ እርምጃው ህጋዊ አይሆንም።

በአንቀጽ 18 (5) ወይም (6) በተመለከተው ምክንያት ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎችን ለማገድ አሠሪው ለእገዳው ምክንያት የሆነው ሁኔታ ባጋጠመው በ3 የሥራ ቀናት ውስጥ ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለስልጣን በጽሑፍ ማስታወቅ አለበት።[2] የግዴታው ዓይነት ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ጉዳዩን እንዲያውቀው ‘በጽሑፍ መንገር’ ቢመስልም በአንቀጽ 20 ውሳኔ ሰጭው አካል ከተሰጠው ስልጣን ይዘት አንጻር ሲታይ ‘ማስታወቅ’ የተባለው ፈቃድ ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ ነው። ምክንያቱም ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን የጽሑፍ ማስታወቂያ በደረሰው በሦስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለእገዳው በቂ ምክንያት ስለመኖሩ እንደሚወስን በድንጋጌው ላይ ተመልክቷል። በቂ ምክንያት ከሌለ ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም ማለት ነው። ሚኒስቴሩ እገዳውን ቢፈቅድም ሊቆይ የሚችለው ቢበዛ ለ90 ቀናት ነው።

ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎችን የማገድ እርምጃ በሚከተሉት ሁኔታዎች ህገ-ወጥ ሊሰኝ ይችላል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው።

  1. የማስታወቅ ግዴታን መጣስ
  2. የሚኒስቴሩን ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ውሳኔ መጣስ

የማስታወቅ ግዴታን መጣስ

አሠሪው ለእገዳው ምክንያት የሆነው ምክንያት ባጋጠመ በሶስት የሥራ ቀናት ውስጥ የጽሑፍ ማስታወቂያ እንዲሰጥ በህግ የተጣለበትን ግዴታ ወደ ጎን በማድረግ የሚወስደው የማገድ እርምጃ ህጋዊነት ይጎድለዋል። ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የማስታወቅ ግዴታ ዋና ዓላማው ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች መታገዳቸውን ለመንገር ሳይሆን በቅድሚያ ፈቃድ ለማግኘት ነው።

የባለስልጣኑን ውሳኔ መጣስ

ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ማስታወቂያ ሲደርሰው ሁለት ነገሮችን ይመረምራል። አንደኛ አሠሪው ያቀረበው ምክንያት በአንቀጽ 18/5/ ወይም /6/ ስር የሚወድቅ መሆኑን ያጣራል። ሁለተኛ ምክንያቱ በድንጋጌው ስር የሚሸፈን እውነት ስለመሆኑ ከማስረጃ ረገድ ይፈትሻል። ሁለቱን በማጣመር ምርምራ ካደረገ በኋላ የሚደርስበት ውሳኔ ጥያቄውን መቀበልና ማጽደቅ ወይም ውድቅ ማድረግ ሊሆን ይችላል። ውድቅ በማድረግ የተሰጠ ውሳኔ ሳይከበር ቀርቶ እገዳው ከቀጠለ ህገ-ወጥ ይሆናል። በይግባኝ ካልተቀየረ በስተቀር ውሳኔውን ወደጎን በማድረግ ማገድ ህጉን ወደ ጎን በማድረግ የተወሰደ ህገ-ወጥ እገዳ ይሆናል። ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን በቂ ምክንያት መኖሩን በማረጋገጥ ጥያቄውን ቢያፀድቀውም ከሚወስነው የእገዳ ጊዜ ወይም በህግ ከተቀመጠው የዘጠና ቀናት ከፍተኛ የእገዳ ጊዜ ካለፈ አሁንም እገዳው ህጋዊነት ይጎድለዋል።

ከላይ በተመለከቱት ሁለት ሁኔታዎች እገዳ ህገ-ወጥ መሆኑ ከተረጋገጠ በውጤት ደረጃ የሥራ ውል እንዳልታገደ ይቆጠራል። ይህም ማለት የታገደው ሠራተኛ ለእገዳው ጊዜ ደመወዙ ተከፍሎት ወደ ሥራው ይመለሳል። ከዚህ በተጨማሪ አሠሪው የሚወስደው ህገ-ወጥ የማገድ እርምጃ በሥራ ውሉ እና በአሠሪና ሠራተኛ ህጉ የተጣለበትን ሥራ የመስጠት እና ደመወዝ የመክፈል ዋነኛ ግዴታ መጣስ እንደመሆኑ ለዚህ ተግባሩ ካሳ ከመክፈል አይድንም። የካሳው አወሳሰን በአሠሪና ሠራተኛ ህጉ ላይ ባይኖርም ጉዳዩ የቀረበለት የሥራ ክርክር ሰሚ አካል የውል ህግ ጠቅላላ ደንቦችን ተፈጻሚ በማድረግ ካሳ መወሰን ይችላል። የውል ህግ ጠቅላላ ደንቦች የሥራ ውልን ጨምሮ በሁሉም ውሎች ተፈጻሚ እንደመሆናቸው በልዩ ውል ባልተሸፈነ ጉዳይ ጠቅላላው ደንብ ተፈጻሚ ይሆናል።


[1] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 22

[2] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 19

Leave a Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s