አዋጅ ቁጥር ፮፻፱/፪ሺ፩ ዓ.ም የተጨማሪ እሴት ታክስ /ማሻሻያ/ አዋጅ

                   አዋጅ ቁጥር ፮፻፱/፪ሺ፩ ዓ.ም.

የተጨማሪ እሴት ታክስ /ማሻሻያ/ አዋጅ

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር ፪፻፹፭/፲፱፻፺፬፺ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፶፭ ንዑስ አንቀፅ /፩/ እና /፲፩/ መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

. አጭርርዕስ
ይህ አዋጅ ‹‹የተጨማሪ እሴት ታክስ /ማሻሻያ/ አዋጅ ቁጥር ፮፻፱/፪ሺ፩›› ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

. ማሻሻያ
የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር ፪፻፹፭/፲፱፻፺፬ እንደሚከተለው ተሻሽሏል፣
፩/ የአዋጁ አንቀጽ ፪ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ተተክቷል፣
‹‹፬/ ‹‹ባለሥልጣን›› ማለት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፤››
፪/ ከአዋጁ አንቀጽ ፪ ሥር የሚከተሉት አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፳፭/ እና /፳፮/ ተጨምረዋል፡፡
‹‹፳፭/ ‹‹የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ›› ማለት የጥሬ ገንዘብ መመዝገቢያ መሣሪያ ወይም የሽያጭ ነቁጣ መሣሪያ ነው፣
‹‹፳፮/ ‹‹አቅራቢ›› ማለት የሽያል መመዝገቢያ መሣሪያዎችን ወይም በመሣሪያው ላይ ተጭኖ አገልግሎት የሚሰጥ ሶፍት ዌርን ወይም ሁለቱንም በአንድ ላይ የሚያቀርብ ሰው ነው፡፡››
፫/ በአዋጁ አንቀጽ ፮ ውስጥ ‹‹በማንኛውም ሰው›› የሚለው ሐረግ ተሰርዞ ‹በማንኛውም የተመዘገበ ሰው›› እንደዚሁም ‹‹ባለማቋረጥ ወይም በመደበኛ ሥራነት›› የሚለው ሐረግ ተሰርዞ ‹‹በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፬/ ከአዋጁ አንቀጽ ፯ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ቀጥሎ የሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፭/ ተጨምሯል፣
‹‹፭/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ሀ/ ተፈፃሚ የሚሆንበት ግብይት ሲከናወን እንደአስፈላጊነቱ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በሚወጣ መመሪያ መሠረት ታክሱ ግዢውን በሚፈፀመው አካል ተይዞ ለባለሥልጣኑ ይከፈላል፡፡››
፭/ የአዋጁ አንቀጽ ፰ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ፊደል ተራ /ሀ/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ፊደል ተራ /ሀ/ ተተክቷል፣
‹‹ሀ. ቢያንስ ሁለት ዓመት ያገለገለ የመኖሪያ ቤት ሽያጭና የመኖሪያ ቤት ኪራይ፣››
፮/ በአዋጁ አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ /፮/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ድንጋጌ›› ተብሎ የተጠቀሰው ተሰርዞ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንኡስ አንቀጽ /፪/ ድንጋጌ›› በሚለው ተተክቷል፣
፯/ በአዋጁ አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ /፯/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ድንጋጌ›› ተብሎ የተጠቀሰው ተሰርዞ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ድንጋጌ›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፰/ በአዋጁ አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ /፰/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፰/ ውስጥ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ/፭/ ድንጋጌ›› ተብሎ የተጠቀሰው ተሰርዞ ‹‹የአንቀጽ ፬ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ድንጋጌ›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፱/ የአዋጁ አንቀጽ ፲፮ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ተተክቷል፡፡
‹‹፫. ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ያለበት ሰው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ሀ/ የተመለከተው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ባለው ወር እስከ መጨረሻ ቀን ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ለ/ የተመለከተው ጊዜ በተጠናቀቀበት ወር እስከ መጨረሻ ቀን ለምዝገባ ማመልከቻ ማቅረብና መመዝገብ አለበት፡፡››
፲/ በአዋጁ አንቀጽ ፳፪ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተተክቷል፣
‹‹፩/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፮/ እና /፯/ በሌላ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር ለተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገበና ታክስ የሚከፈልበት ግብይት የሚያካሂድ ሰው ደረሰኝ ወዲያውኑ መስጠት አለበት፡፡ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ያልተመዘገበ ሰው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መስጠት አይችልም፡፡››
፲፩/ የአዋጁ አንቀጽ ፳፪ ንዑስ አንቀጽ /፫/ ተሰርዞ ንዑስ አንቀጽ /፬/፣ /፭/፣ /፮/ እና /፯/ እንደ ቅደም ተከተላቸው ንዑስ አንቀጽ /፫/፣ /፬/፣ /፭/ እና /፮/ ሆነዋል፡፡
፲፪/ የአዋጁ አንቀጽ ፳፮ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ተተክቷል፣
‹‹፩/ እያንዳንዱ የተመዘገበ ሰው፣
ሀ/ በአንድ የሂሳብ ጊዜ ውስጥ ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለበት ቢሆንም ባይሆንም በእያንዳንዱ የሂሳብ ጊዜ ሂሳቡን ግብር ባለሥልጣኑ ዘንድ በመቅረብ ወይም በኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ዘዴ ወይም ባለሥልጣኑ ለሚወክለው የፋይናንስ ተቋም ማስታወቀ፣ እና
ለ/ ለእያንዳንዱ የሂሳብ ጊዜ የተሰጠውን የመጨረሻ ታክስ መክፈያ ጊዜ ገደብ ጠብቆ ለባለሥልጣኑ ወይም ባለሥልጣኑ ለወከለው ሰው ከገቢ ማስታወቂያው ጋር በአንድነት ታክሱን መክፈል አለበት፡፡››
፲፫/ ከአዋጁ አንቀጽ ፴ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ቀጥሎ የሚከተሉት አዲስ ንዑስ አንቀጾች /፫/፣ /፬/ እና /፭/ ተጨምረዋል፣
‹‹፫/ በታክስ ከፋዩ የንግድ ሥራ ቦታ በመገኘት ምርመራ ለማድረግ ሥልጣን የተሰጣቸው የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ማናቸውንም ሕገ ወጥ ደረሰኝ ወይም የሂሳብ ሰነድ ወይም የሂሳብ መዝገብ ካገኙ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳያስፈልግ ሕገወጥ የሆነውን ደረሰኝ ወይም ሰነድ መያዝ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተያዘ ወይም የተገኘ ሰነድ በማስረጃነት በፍርድ ቤት ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡
፬/ ሕገወጥ ደረሰኞችን ወይም ሰነዶችን ለመስጠት ፍቃደኛ ባልሆነ ግብር ከፋይ ላይ የፖሊስ ኃይል በመጠቀም ማስገደድ ይቻላል፡፡
፭/ ለዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፫/ አፈፃፀም በባለሥልጣኑ ሠራተኛ ትብብር የተጠየቀ ማናቸውም የፖሊስ ኃይል አባል የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡
፲፬/ የአዋጁ አንቀጽ ፵፪ ተሰርዞ በሚከተለው አዲስ አንቀጽ ፵፪ተተክቷል፣

‹‹፵፪/ መቀጫንስለማንሳት
፩/ ባለሥልጣኑ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በታክስ ከፋይ ላይ የተጣለ አስተዳደራዊ መቀጫ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲነሳ ለማድረግ ይችላል፡፡
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፩/ መሠረት የሚነሳው መቀጫ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፵፯ መሠረት የሚታሰበውን ወለድ አይጨምርም፡፡››
፲፭/ በአዋጁ አንቀጽ ፵፫ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ውስጥ ‹‹የሚፈለግበትን ታክስ ካልከፈለ›› ከሚለው ሐረግ ቀጥሎ ‹‹ወይም ይግባኝ ካላቀረበ›› የሚል ሐረግ ተጨምሯል፡፡
፲፮/ የአዋጁ አንቀጽ ፵፭ ንዑስ አንቀጽ /ሀ/፣ /ለ/፣ /ሐ/ እና /መ/ የንዑስ አንቀጽ /፩/ ፊደል ተራ /ሀ/፣ /ለ/፣ /ሐ/ እና /መ/ ሆነው የሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፪/ ተጨምሯል፣
‹‹፪/ ለዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩/ለ/ አፈጻጸም ‹‹ሀሰተኛ ደረሰኝ›› ማለት በባለሥልጣኑ ሳይፈቀድ የታተመ ወይም በኮምፒውተር የተዘጋጀ ደረሰኝ ወይም የግዢውን ወይም የሽያጩን ሂሣብ ለማሳነስ ወይም ለመጨመር በማሰብ ወይም በቸልተኛነት በሰነዱ ላይ አሀዝ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይም ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ በማተም ወይም በማባዛት ወይም ሁሉንም ቅጂዎች እንደበራሪ መጠቀም ወይም የሚፈቀደው የታክስ ተቀናሽ ወይም የተመላሽ ሂሣብ እንዲጨምር ወይም የማይገባውን ተመላሽ ለማግኘት ወይም ሌላ ማናቸውም የማጭበርበር ተግባር ለመፈጸም የተዘጋጀ ሰነድ ነው፡፡››
፲፯/ ከአዋጁ አንቀጽ ፵፮ ንዑስ አንቀጽ /፬/ ቀጥሎ የሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፭/ ተጨምሯል፣
‹‹፭/ ማናቸውም ታክስ ከፋይ በማንኛውም የሂሳብ ጊዜ ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ባይኖረውም የታክስ ማስታወቂያ ካላቀረበ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንጽ ፬/ሀ/ መሠረት ይቀጣል፡፡››
፲፰/ ከአዋጁ አንቀጽ ፵፯ ቀጥሎ የሚከተሉት አዲስ አንቀጽ ፵፯ሀ፣ ፵፯ለ እና ፵፯ሐ ተጨምረዋል፣

‹‹፵፯ሀየሽያጭመመዝገቢያመሣሪያአጠቃቀምግዴታዎችንባለመወጣትየሚጣልመቀጫ
ማንኛውም በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የመጠቀም ግዴታ ያለበት ሰው፣
፩/ ዕውቅና ያልተሰጠው ወይም በባለሥልጣኑ ዘንድ ያልተመዘገበ መሣሪያ ወይም የሽያጭ ነቁጣ ሶፍትዌር ሲጠቀም ከተደረሰበት ለተጠቀመበት ለእያንዳንዱ መሣሪያ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፪/ መሣሪያው በጥገና ላይ ባለበት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከታተመ ደረሰኝ ውጪ በሌላ ማናቸውም ዓይነት ደረሰኝ ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፫/ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም የፊሲካል ማስታወሻው እንዲቀየር ያደረገ ወይም ጉዳት ለማድረስ ወይም ማስታወሻውን ለመቀየር ሙከራ ያደረገ ከሆነ ብር ፩፻ሺ ይቀጣል፣
፬/ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያን ሥርዓት ኦዲት እንዳያደርግ መሰናክል ከፈጠረ ወይም በመሳሪያው ላይ በዓመት አንድ ጊዜ በአገልግሎት ማዕከል የቴክኒክ ምርመራ ካላስደረገ ብር ፳፭ሺ ይቀጣል፣
፭/ በንግድ ሥራው ለሚጠቀምበት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከአገልግሎት ማዕከል ጋር ውል ካልፈጸመ ወይም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያውን ከተርሚናል ጋር ሳያያይዝ ከተጠቀመ ወይም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው የምርመራ መዝገብ ከመሣሪያው ጎን እንዲቀመጥ ካላደረገ ወይም በሽያጭ መመዝገቢያ የተመዘገቡ ዕቃዎች ተመላሽ መደረጋቸው ወይም ደንበኛው የተመላሽ ጥያቄ ማቅረቡ በተመላሽ መዝገብ ላይ በትክክል መመዝገቡ ሳይረጋገጥ የተመላሽ ደረሰኝ ከሰጠ ብር ፳፭ሺ ይቀጣል፣
፮/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው በስርቆት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ አገልግሎት መስጠት ሲያቋርጥ በሦስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ወይም በሌላ ማናቸውም ምክንያት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው ብልሽት ባጋጠመው በሁለት ሰዓት ውስጥ ለአገልግሎት ማዕከሉና ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፹ሺ ይቀጣል፣
፯/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የሚቀመጥበትን የንግድ ቦታ ትክክለኛ አድራሻ ለባለሥልጣኑ ያላስታወቀ እንደሆነ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፰/ የአድራሻ ወይም የስም ለውጥ ሲያደርግ ወይም የንግድ ሥራውን የሚያቋርጥ ሲሆን ከሦስት ቀናት አስቀድሞ ለአገልግሎት ማዕከሉና ለባለሥልጣኑ ያላስታወቀ እንደሆነ ብር ፳፭ሺ ይቀጣል፣
፱/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው ጥቅም ላይ በሚውልበት የንግድ ሥራ ቦታው፣
ሀ/ የተጠቃሚውን ስም፣ የንግድ ስም፣ የንግዱ ሥራ የሚካሄድበትን አድራሻ፣ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያውን የዕውቅና እና የመጠቀሚያ ፈቃድ ቁጥር፣
ለ/ ‹‹የሽያጭ ሠራተኞች መሣሪያው የተበላሸ ከሆነ በባለሥልጣኑ ፈቃድ የታተመ ተከታታይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ ለደንበኛው የመስጠት ግዴታ አለባቸው›› የሚል ማስታወቂያ፣ እና
ሐ/ ‹‹ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ አይክፈሉ›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ማስታወቂያ፣ በግልጽና በሚታይ ቦታ ለጥፎ ካልተገኘ ብር ፲ሺ ይቀጣል፣
፲/ ሥራ ላይ የዋለውን የሽያጭ ነቁጣ ሶፍት ዌር ባለሥልጣኑ ዕውቅና ባልሰጠው ሰው እንዲቀየር ወይም እንዲሻሻል ካደረገ ብር ፴ሺ ይቀጣል፡፡

፵፯ለየአቅራቢነትግዴታዎችንባለመወጣትየሚጣልመቀጫ
ማንኛውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ወይም ሶፍትዌር አቅራቢነት ዕውቅናና ፈቃድ የተሰጠው ሰው፣
፩/ የንግድ ሥራውን የአድራሻ ለውጥ ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፩፻ሺ ይቀጣል፣
፪/ በባለሥልጣኑ ዕውቅና ያልተሰጠውን የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ለገበያ ካዋለ ብር ፭፻ሺ ይቀጣል፣
፫/ ለእያንዳንዱ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ምዝገባ ከባለሥልጣኑ የመሣሪያ መለያ ቁጥር ካልወሰደ ወይም የወሰደውን የመሣሪያ መለያ ቁጥር ለእይታ በሚያመች ቦታ በመሣሪያው ላይ ካልለጠፈ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፬/ በሥራ ላይ ባሉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ላይ የሚያደርገውን ማናቸውም ለውጥ ለባለሥልጣኑ በቅድሚያ ካላስታወቀ ወይም ስለ መሣሪያው አጠቃቀም በሚያብራራው የአጠቃቀም መመሪያ ውስጥ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ካስገባ ወይም ትክክለኛውን መረጃ ከቀነሰ ብር ፩፻ሺ ይቀጣል፣
፭/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በመሰረቃቸው ወይም ሊጠገኑ በማይቻልበት ሁኔታ በአደጋ ምክንያት ብልሽት የደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀው እንዲተኩላቸው ለሚጠይቁ የአገልግሎት ማዕከላት በሦስት ቀናት ውስጥ ለማቅረብ አለመቻሉን ለባለ ሥልጣኑ አስቀድሞ ካላስታወቀ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣
፮/ ውል ስለተዋዋላቸው የአገልግሎት ማዕከላት መረጃ ካልያዘ ወይም ውላቸውን ስላቋረጡ ወይም አዲስ ስለተዋዋላቸው የአገልግሎት ማዕከላት ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፶ሺ ይቀጣል፣

፵፯ሐየአገልግሎትማዕከልግዴታዎችን ባለመወጣትየሚጣልመቀጫ
ማናቸውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች የአገልግሎት ማዕከል፣
፩/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የፊሲካል ማስታወሻ በተተካ በሁለት ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ብር ፳ሺ ይቀጣል፣
፪/ ውል የገባባቸውን የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በዓመት አንድ ጊዜ የቴክኒክ ምርመራ ካላደረገ ብር ፳ሺ ይቀጣል፣
፫/ አቅራቢው ዕውቅና ሳይሰጠውና በባለሥልጣኑ ዘንድ ሳይመዘገብ በሥራ ላሰማራው ለእያንዳንዱ ሠራተኛ ብር ፶ሺ ይቀጣል፡፡››
፲፱/ ከአዋጁ አንቀጽ ፶ ቀጥሎ የሚከተሉት አዲስ አንቀጽ ፶ሀ፣ ፶ለ፣ ፶ሐ፣ ፶መ፣ ፶ሠ፣ እና ፶ረ፣ ተጨምረዋል፣

‹‹፶ሀ. ለተጨማሪእሴትታክስከፋይነትአለመመዝገብ
ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት የመመዝገብ ግዴታ ያለበት ሆኖ ሳይመዘገብ የተገኘ ግብር ከፋይ ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፲ሺ እስከ ብር ፶ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እሥራት ይቀጣል፡፡
፶ለ. የተጨማሪ እሴት ታክስ ባልሆነ ደረሰኝ
ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ማካሄድ
፩/ ማንኛውም ለተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገበ ሰው ያለተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ግብይት ሲያካሂድ ከተገኘ ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፲ሺ በማያንስ እና ከብር ፩፻ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጫ እና ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት ይቀጣል፡፡
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /፩/ በተጠቀሰው ሕገወጥ ደረሰኝ ላይ በተመለከተው የገንዘብ መጠን መሠረት መከፈል የነበረበት ታክስ ከብር ፩፻ሺ በላይ ከሆነ የሚጣለው የገንዘብ ቅጣት የታክሱን መጠን ያህል ይሆናል፡፡

፶ሐ. ያልተፈቀደደረሰኝመጠቀምወይምማተም
ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ሳይሰጥ በኮምፒውተር የተዘጋጀ ደረሰኝ ወይም ደረሰኝ በማሳተም የተጠቀመ ወይም የደረሰኝ ሕትመት አገልግሎት የሰጠ ሰው ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፲ሺ እስከ ብር ፩፻ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት ያስቀጣል፡፡

፶መ. የሽያጭመመዝገቢያመሣሪያአጠቃቀምን በሚመለከትስለሚፈጸምጥፋት
ማንኛውም በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የመጠቀም ግዴታ ያለበት ሰው፡-
፩/ በባለሥልጣኑ ዕውቅና ያልተሰጠው ወይም ያልተመዘገበ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከተጠቀመ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፪/ መሣሪያው በጥገና ላይ ባለበት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከታተመ ደረሰኝ ውጪ ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፫/ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው የፊሲካል ማስታወሻ ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም የፊሲካል ማስታወሻው እንዲቀየር ያደረገ ወይም ጉዳት ለማድረስ ወይም ማስታወሻውን ለመቀየር ሙከራ ያደረገ ከሆነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፬/ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያውን ሥርዓት ኦዲት እንዳያደርግ መሰናክል የፈጠረ ወይም በመሣሪያው ላይ በዓመት አንድ ጊዜ በአገልግሎት ማዕከል የቴክኒክ ምርመራ ያላስደረገ ከሆነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከስድስት ወር በማያንስና ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፭/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያው የሚገኝበትን የንግድ ቦታ ትክክለኛ አድራሻ ለባለሥልጣኑ ያላስታወቀ እንደሆነ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከስድስት ወር በማያንስና ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡

፶ሠ. በአቅራቢያዎችየሚፈጸሙጥፋቶች
ማንኛውም በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ወይም ሶፍትዌር አቅራቢነት ዕውቅናና ፈቃድ የተሰጠው ሰው፡-
፩/ የንግድ ሥራውን የአድራሻ ለውጥ ለባለሥልጣኑ ካላስታወቀ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፪/ በባለሥልጣኑ ዕውቅና ያልተሰጠውን መሣሪያ ለገበያ ካዋለ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፣
፫/ በሥራ ላይ ባሉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ላይ የሚያደርገውን ማናቸውም ለውጥ ለባለሥልጣኑ በቅድሚያ ካላስታወቀ ወይም በመሣሪያው የአጠቃቀም መመሪያ ውስጥ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ካስገባ ወይም ትክክለኛውን መረጃ ከቀነሰ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡

፶ረ. በሽያጭመመዝገቢያመሣሪያዎች የአገልግሎትማዕከልናሠራተኞችየሚፈጸሙጥፋቶች
፩/ ማናቸውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች የአገልግሎት ማዕከል አቅራቢው ዕውቅና ያልሰጠውንና በባለሥልጣኑ ዘንድ ያልተመዘገበ ሠራተኛ በሥራ ላይ አሰማርቶ ከተገኘ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡
፪/ ማናቸውም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች የአገልግሎት ማዕከል ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያን ያለአገልግሎት ማዕከሉና ያለባለሥልጣኑ ዕውቅና ከፈታታ ወይም ከገጣጠመ ወይም የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ሳይበላሽ ሆን ብሎ እሽጉን ካነሳ ወይም አካሉን ከቀየረ ወይም እነዚህን የመሳሰሉ አድራጎቶች ከፈጸመ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፭ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጫ እና ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡››
፳/ በአዋጁ አንቀጽ ፶፩ ንዑስ አንቀጽ /፩/ ውስጥ ‹‹በ፪ /ሁለት/ ዓመት እስራት›› የሚለው ሐረግ ተሰርዞ ‹‹ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት›› በሚለው ተተክቷል፡፡
፳፩/ የአዋጁ አንቀጽ ፶፫ ንዑስ አንቀጽ /፪/ እና /፫/ የነበሩት ንዑስ አንቀጽ /፬/ እና /፭/ ሆነው የሚከተሉት አዲስ ንዑስ አንቀጽ /፪/ እና /፫/ ተጨምረዋል፣
‹‹፪/ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች አጠቃቀም ደንብና መመሪያዎችን በመተላለፍ፣
ሀ/ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የፈታታ ወይም የገጣጠመ ወይም የሰርቪስ ሠራተኛ በሌለበት ሥራ ላይ እንዲውል የፈቀደ ወይም የመሣሪያውን መለያ ቁጥር ያቀያየረ እንደሆነ፣ ወይም
ለ/ በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ተጠቃሚው ወይም በአገልግሎት ማዕከሉ ወይም በሠራተኛው ወይም በአቅራቢው የተፈጸመን ማናቸውንም ሕገ ወጥ አድራጎት እያወቀ ወይም በቸልተኝነት በ፳፬ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ለባለሥልጣኑ ሪፖርት ያላደረገ እንደሆነ፣
ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከብር ፭ሺ በማያንስና ከብር ፲ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጫ እና ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡
፫/ የግብር ባለሥልጣኑ ሠራተኛ ያለ በቂ ምክንያት ጉዳይን በማጓተት በግብር ከፋይ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት በፍትሐ ብሔር ያለበት ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ጥፋተኛነቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ እሥራት ይቀጣል፡፡››

. አዋጁየሚፀናበትጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ታህሣሥ ፲፮ ቀን ፪ሺ፩ ዓ.ም.
ግርማ ወልደጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ  ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

ጠጥቶ ፈረስ መንዳት

ጠጥቶ መንዳት ክልክል ነው፡፡ ይህን ህግ ጠጥተው የማውቁ ሆነ ነድተው የማውቁ ሁሉ ያውቁታል፡፡ ግን ምን መንዳት ነው የተከለከለው? ለምሳሌ የሚነዳው መኪና መሆኑ ቀርቶ ፈረስ ቢሆንስ? በአሜሪካ ፔንስላቫኒያ ግዛት ፍርድ ቤት በቀረበ ጉዳይ ላይ ይኸው ነጥብ ሁሉንም ዳኞች ባያስማማም ፈረስም፤ መኪናም ያው ነው የሚል አቋም ተይዞ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡ (Pennsylvania v. Noel, 857 A.2d 1283 (Pa. 2004) (Eakin, J., dissenting). ) ፍርዱ የተሰጠው እንደሚከተለው በግጥም ነበር፡፡

A horse is a horse, of course, of course,
but the Vehicle Code does not divorce
its application from, perforce,
a steed, as my colleagues said.
“It’s not vague” I’ll say until I’m hoarse,
and whether a car, a truck or horse
this law applies with equal force,
and I’d reverse instead.

የስራ መሪ – የፍርድ ቤት ስልጣን (የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ ክፍል ሁለት)

የስራ መሪ – የፍርድ ቤት ስልጣን

ላይ ላዩን ሲታይ የስራ መሪ የሚያቀርበውን ክስ ለማየት የዳኝነት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት መለየት ቀላል ቢመስልም የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 የፍርድ ቤቶችን ስልጣን በተመለከተ እልባት ሳይሰጥ በቸልታ ካለፈው መሰረታዊ ጥያቄ አንጻር ሲታይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት ምክንያትን መሰረት ያደረገ ጥልቅ ፍተሻ ማድረግ እንዳለባቸው ይጠቁመናል፡፡

ከአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 ክፍል ሁለት ድንጋጌዎች በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አዋጁ የአሰሪና ሰራተኛ ፍርድ ቤቶችን አያቋቁምም፡፡ የአዋጁ ክፍል ሁለት ርዕስ የአማርኛ ምንባብ ‘ስለ ስራ ክርክር ችሎቶች’ በሚል የተቀመጠ ሲሆን ከዚህ በተቃራኒ የእንግሊዝኛው ቅጂ Labour Courts የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል፡፡ በይዘትም ሆነ በተፈጻሚነት ወሰን ረገድ የስራ ክርክር ችሎቶች እና Labour Courts እጅግ የተራራቁ ናቸው፡፡ Labour Courts በህጋዊ ሰውነት፤ በአደረጃጀት በሰራተኛ ቅጥርና አስተዳደር ብሎም በበጀት አስተዳደር ከመደበኛው ፍርድ ቤት በተለየ መንገድ በራሳቸው የሚመሩና የራሳቸው መዋቅርና ፕሬዚደንት ያላቸው በልዩ ህግ የሚቋቋሙ ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ በአንጻሩ የስራ ክርክር ችሎቶች በመደበኛው ፍርድ ስር እንደ አንድ ልዩ ችሎት የተዋቀሩ ከመሆናቸውም ባሻገር በውስጥ አደረጃጀት ሆነ በመዋቅር ደረጃ ራሳቸውን ችለው የቆሙ አሊያም የተቋቋሙ የዳኝነት አካላት አይደሉም፡፡

የአዋጁ ክፍል ሁለት የአማርኛ ሆነ የእንግሊዝኛ ዝርዝር ድንጋጌዎች ስለ ስራ ክርክር ችሎቶች የሚያወሩ እንደመሆናቸው በዚህ ረገድ ሊፈጠር የሚችል ውዥንብር አይኖርም፡፡ ሆኖም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ የስራ ክርክር ችሎቶች እንጂ የስራ ክርክር ፍርድ ቤቶች እንዳልተቋቋሙ ልብ ልንል ይገባል፡፡

የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 137 በሁሉም ክልሎች በሶስት ደረጃ የተዋቀሩ የስራ ክርክር ችሎቶች እንደሚኖሩ ይገልጻል፡፡ እነዚህም፤

ሀ. የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት

ለ. ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት ይግባኝ የሚሰማ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት

ሐ. የማዕከላዊ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት

አዋጁ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ደረጃ ስለሚታዩ ወይም ሊታዩ ስለሚገባቸው  የስራ ክርክሮች በተመለከተ በዝምታ ብቻ ሳይሆን በቸልታ ማለፍን መርጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ሰለሚፈጠሩ የስራ ክርክሮችም በየትኛው ፍርድ ቤት ወይም ችሎት እንደሚታዩ አዋጁ በቂ ምላሽ አይሰጥም፡፡

የክልል የመጀመሪያ ደረጅ ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት የዳኝነት ስልጣን በየክልሉ በተመዘገቡ የክልል የንግድ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች የሚያቀርቡትን የስራ ክርክር ብቻ ይሁን በፌደራል መንግስት በተመዘገቡ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ የተቀጠሩ ሰራተኞች የሚያቀርቡትን የስራ ክርክር ጭምር ስለመሆኑ ከአዋጁ ፍንጭ እንኳን ማግኘት ያዳግታል፡፡ በፌደራልና በክልል የስራ ክርክር መካከል ያለው ክፍፍል በድሬዳዋና በአዲስ አበባም የሚከሰት ነው፡፡

በሁለቱም መስተዳደሮች ውስጥ በፌደራልና በየመስተዳደሩ ተለይተው በተመዘገቡ አሰሪዎችና ሰራተኞች ራሳቸውን የቻሉ የስራ ክርክሮች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች እነዚህን የስራ ክርክሮች ያለልዩነት ማየት ይችላሉ ቢባል እንኳን አዋጁ የስራ ክርክር ችሎቶችን ያቋቋመው በክልል ደረጃ ብቻ እንደመሆኑ አሰሪው፤ሰራተኛው ብሎም የስራ መሪ የሚያቀርቡት ክስ ለስራ ክርክር ችሎት ቀርቧል? አልቀረበም? በሚል ጭብጥ ተይዞ የፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ውሳኔ መስጠት የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ ሊሆን አይችልም፡፡

የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 20 እና 23 በፌደራል በመጀመሪያ፤ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፍትሐ ብሔር፤ የወንጀል እና የስራ ክርክር ችሎቶች እንደሚኖሩ ይደነግጋል፡፡ የስራ ክርክር (Labour Dispute) ሲባል ከአዋጅ ቁጥር 377/96 ባለፈ ማናቸውንም ከአሰሪና ሰራተና ግንኙነት የሚመነጩ የስራ ክርክሮች ያቅፋል፡፡

በሰበር ችሎት ያለው አቋም

ክሱን ያቀረበው ከሳሽ የስራ መሪ መሆኑ ከተረጋገጠ በጉዳዩ ላይ የዳኝነት ስልጣን ያለውን ፍርድ ቤትና ተፈጻሚ የሚሆነውን ህግ መለየት በቀጣይነት እልባት ማግኘት ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ክፍል ሁለት የዳኝነት ስልጣን በተመለከተ የሰበር ችሎት በሚከተለው መልኩ አስገዳጅነት ያላቸውን ውሳኔዎች ሰጥቷል፡፡

በሰበር ከተሰጡት ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ሰራተኛ ነኝ በሚል እምነት ክሱን ለስራ ክርክር ችሎት ያቀረበ ከሳሽ በአሰሪው የሚነሳን መቃወሚያ መሰረት በማድረግ ችሎቱ ከሳሽ የስራ መሪ እንጂ ሰራተኛ እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ የደረሰ እንደሆነ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም ብሎ መዝገቡን መዝጋት ይኖርበታል፡፡ ከሳሽ በስር ፍርድ ቤት ሰራተኛ ተብሎ በይግባኝ ውሳኔው ተሸሮ የስራ መሪ ነው የሚል አቋም በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተያዘ እንደሆነም በቀጣይነት መዝገቡን መዝጋት እንጂ ለስራ መሪ ተፈጻሚ በሚሆነው ህግ ውሳኔ ሊሰጥ አይችልም፡፡

በአመልካች የአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ አ.ማ እና ተጠሪ አቶ ከበደ ወንድሙ (የሰ.መ.ቁ. 41321 የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም) መካከል በሰበር በቀረበ ክርክር ላይ ተጠሪው በአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ  ለረጅም ዓመታት የምርት ጥራት ቁጥጥርና አገልግሎት ኃላፊ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ፀሐፊ ሆኖ ሲሰራ ለ19 ዓመታት ካገለገለበት ድርጅት የሥራ ውሉን  አመልካች (በስር ፍርድ ቤት ተከሳሽ) ከሕግ ውጪ ያቋረጠው በመሆኑ የአንድ ወር ከ14 ቀን ደመወዝ ተከፍሎት ወደሥራ እንዲመለስ ውሳኔ እንዲሰጠው ዳኝነት የጠየቀ ሲሆን አመልካቹም “ከሣሽ የሥራ መሪ እንጅ ሠራተኛ አይደለም፤ ጉዳዩ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ሊታይ አይገባም” በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና ስንብቱም በሥራ መመሪያዎች መሠረት ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆኑና እምቢተኛ በመሆኑ በአግባቡ ነው በማለት በአማራጭ ተከራክሯል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተጠሪ የሥራ መሪ አይደለም በማለትና የመቃወሚያውን ክርክር ውድቅ በማድረግ የሥራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ ውጪ ስለሆነ የ1 ወር ከ14 ቀን ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ሥራ ይመለስ ሲል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሣኔ ላይ ይግባኝ የቀረበለት የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪው የሥራ መሪ ነው ነገር ግን ስንብቱ ከሥራ መሪዎች መተዳዳሪያ ደንብ አንቀጽ 1ዐ.5.2 ድንጋጌ ውጪ ነው በማለት ውሉ ተቋርጦ ለቆየበት ጊዜ ያልተከፈለው ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ሥራ ይመለስ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የስር ፍርድ ቤቶች በሰጡት ውሳኔ ላይ ቅር በመሰኘት አመልካች ባቀረበው የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የሥራ መሪ ከመሆኑ አንፃር የሥራ ክርክር ችሎት ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የላቸውም ተብሎ እንዲሻርለት መከራከሪያውን አቅርቧል፡፡ የሰበር ችሎቱም በአመልካች የቀረበውን መከራከሪያ በመቀበል ይግባኙን የሰማው ፍርድ ቤት ተጠሪ የስራ መሪ መሆኑን ካረጋገጠ የዳኝነት ስልጣን እንደሌለው ገልጾ መዝገቡን መዝጋት እንደነበረበት ካተተ በኋላ ውሳኔውን ሽሮታል፡፡

በሰበር ውሳኔው ላይ በተሰጠው ሀተታ ላይ እንደተመለከተው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተጠሪ“የሥራ መሪ መሆኑን ካረጋገጠና ውሣኔ ከሰጠ ወደ ሌላ ጭብጥ መሄድ የሚጠበቅበት አልነበረም፡፡ የሥራ መሪ መሆኑ ከተረጋገጠና ውሣኔ ከተሰጠ የሥራ መሪዎች ጉዳይ ዳኝነት ሊታይ የሚችለው በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት በሥራ ክርክር ሂደትና ችሎት ሣይሆን በፍትሐብሔር ሕግ በተመለከቱ ሥርዓቶች መሠረት ነው፡፡”

በተመሳሳይ መልኩ በአመልካች የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና ተጠሪ ወ/ሮ ንግሥት ለጥይበሉ (የሰ.መ.ቁ. 42901) ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም በሰበር ታይቶ በተሰጠ ውሳኔ ጉዳዩ በመጀመሪያ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠሪ የስራ መሪ ነች በሚል በአመልካች የቀረበለትን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏት ወደ ስራ እንድትመለስ ውሳኔ ሰጥቶ ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ውሳኔውን በማጽናቱ በአመልካች የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎት ተጠሪ የስራ መሪ ነች የሚል መደምደሚያ ላይ በመድረሱ ተጠሪ በሥራ ክርክር ችሎት ክስ ለማቅረብም ሆነ ክርክር ለማካሄድና ዳኝነት ለማግኘት የምትችልበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን በማተት የመጀመሪያ ደረጃ እና ከፍተኛ ፍ/ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

የሰበር ችሎት ይህን አቋሙን ወጥነት ባለው መልኩ ተፈጻሚ በማድረግ በአመልካች የሸዋ ጥጥ ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ተጠሪ አቶ ታከለ ቀፀላ (የሰ.መ.ቁ.39658) መካከል በነበረው ክርክር የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በሕብረት ስምምነት የስራ መሪ ስለተደረጉ የስራ መሪ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሰ በኋላ በዚሁ መሰረት የስር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ለማየት ስልጣን እንደማይኖራቸው በመግለጽ የሰጧቸውን ውሳኔዎች ሽሯቸዋል፡፡

በአመልካች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ አቶ ሙሊት ታረቀኝ (የሰ.መ.ቁ.36894) በነበረው ክርክርም ታህሳስ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የዳኝነት ስልጣንን በተመለከተ ተመሳሳይ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

መሰረታዊው ጥያቄ

ከለይ በሰበር ከተሰጡት ውሳኔዎች የስራ ክርክር ችሎት ትርጉምን በተመለከተ መሰረታዊ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ በክልል ደረጃ የስራ ክርክር ችሎቶች የተቋቋሙት በአዋጅ ቁጥር 377/96 እንደመሆኑ እነዚህ ችሎቶች በአዋጁ መሰረት በሰራተኛና በአሰሪ ወይም በማህበሮቻቸው ለሚቀርቡ ክሶች ዳኝነት የሚሰጡ የፍርድ አካለት እንደሆኑ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል ስለሆነም በስራ መሪ የሚቀርቡ ክሶችን በተመለከተ የዳኝነት ስልጣን የላቸውም ወደሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል ይሁን እንጂ በዚህ ድምዳሜ እርግጠኛ ለመሆን የየክልሉ የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በቀጥታ የስራ ክርክር ችሎቶችን አለማቋቋማቸው ማመሳከር ያስፈልጋል

በክልል ደረጃ የክልሉ የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የስራ ክርክር ችሎቶን አቋቁሞ እንደሆነ በስራ መሪ የሚቀርብ ክስ የስራ ክርክር ሳይሆን የፍትሀ ብሔር እንደሆነ መውሰዱ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው ምክንያቱም የስራ ክርክር ተብሎ የስልጣኑ ወሰን በግልጽ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ማዕቀፍ ውስጥ እስካልተገደበ ድረስ የስራ ክርክርን ከአዋጅ 377/96 ጋር ብቻ ማቆራኘቱ ከአዋጅ ቁጥር 377/96 ውጪ አሰሪና ሰራተኛ የሚባል ነገር የለም የማለት ያህል ነው ከዚህ ሓሳብ ጋር ለመስማማትም ሆነ ላለመስማማት የስራ ክርክር ለሚለው ቃል ተገቢውን ፍቺ መስጠት ይኖርብናል፡፡

ፍተሻችን የበለጠ ግልጽ እንዲሆን በፌደራል ደረጃ የስራ ክርክር ችሎት የሚለው ቃል ምን እንደሚወክል እንዳስሳለን ከላይ ግልጽ ለማድረግ እንደሞከርኩት አዋጅ ቁጥር 377/96 በፌደራል ደረጃ የስራ ክርክር ችሎቶችን አያቋቁምም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በፌደራል በመጀመሪያ፤ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የስራ ክርክር ችሎቶች እንደሚኖሩ የተደነገገው በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 20 እና 23 ላይ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ በአዋጁ የሚቋቋሙት የስራ ክርክር ችሎቶች የሚያስተናግዷቸው ጉዳዮች ከአዋጅ 377/96 የሚመነጩትን ብቻ ስለመሆኑ በግልጽ ሆነ በተዘዋዋሪ የተመለከተ ነገር የለም፡፡ የስራ ክርክር ሲባልም ማናቸውም የስራ ውልን መሰረት አድርገው የሚነሱ ክርክሮችን በሙሉ የሚያጠቃልል እንጂ በአዋጅ 377/96 መሰረት ከተደረጉ የስራ ውሎች የሚመነጩ ክርክሮች እንደሆነ ተደርጎ አለአግባብ ጠባብ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

የስራ መሪ ከአዋጅ 377/96 ተፈጻሚነት ወሰን ውጪ እንዲሆን የተደረገው ከአሰሪው ጋር የስራ ውል ስለሌለው ሳይሆን በሰራተኞችና መካከል ሊፈጠር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስወገድ ከሚል የፖሊሲ አቋም የተነሳ ነው ስለሆነም የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ.377/96 በስራ መሪ ላይ ተፈጻሚነት የሌለው መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 የተቋቋሙት የስራ ክርክር ችለቶች በስራ መሪ የሚቀርቡ ክሶችን ለማየት የዳኝነት ስልጣን ያጣሉ ማለት አይደለም፡፡

በስራ መሪ የሚቀርቡ ክሶች ላይ በተግባር ተፈጻሚ እየተደረጉ ያሉት ድንጋጌዎች በፍትሐ ብሔር ህጉ ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም በዋነኛነት በስራ በውል ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነትን የሚገዙ ድንጋጌዎች ናቸው ከዚህ ህግ የሚመነጩ ክርክሮችም በባሕሪያቸው የስራ ክርክሮች እንጂ የፍትሐ ብሔር በሚል ድፍን ያለ ፍረጃ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የስራ ክርክር ችሎቶችን የዳኝነት ስልጣን የሚያሳጣ በቂ ምክንያት አይደለም፡፡

በፍትሐ ብሄር ህጉ ውስጥ የተቀመጡት የአሰሪና ሰራተኛ ግኑኘትን የሚመሩት ድንጋጌዎቸ “የፍትሐ ብሄር ህግ” በሚለው ስር በመገኘታቸው ብቻ በስራ መሪ የሚቀርብ ክስም በፍትሐ ብሄር ችሎት መታየት እንዳለበት የፍትሐ ብሄር ክርክር አድርጎ መውሰዱ መሰረታዊውን ጥያቄ መሸሽ እንጂ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አይደለም የአንድ ክርክር ዓይነት ሊወሰን የሚገባው በይዘቱ እንጂ በሚገኝበት መጽሐፍ መሰረት አይደለም፡፡

ስለሆነም ከሳሽ ሰራተኛ ነኝ በሚል እምነት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ከሳሽ የስራ መሪ እንጂ ሰራተኛ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ በሚደርስበት ጊዜ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96ን ተፈጻሚነት በማስቀረት ተፈጻሚነት ባለው ሌላ ህግ ውሳኔ መስጠት እንጂ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም በማለት የቀረበለትን ክስ ወዲያውኑ ሊዘጋው አይገባም፡፡

ከሳሽ በስር ፍርድ ቤት ሰራተኛ ተብሎ በይግባኝ ውሳኔው ተሸሮ የስራ መሪ ነው የሚል አቋም በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተያዘ እንደሆነም በቀጣይነት ለስራ መሪ ተፈጻሚ በሚሆነው ህግ ውሳኔ መስጠት እነጂ መዝገቡን ሊዘጋው አይገባም፡፡

ስለሆነም ከላይ በቀረበው የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ዳሰሳ ላይ ክሱ ከመጀመሪያውኑ ለፌደራል ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት የቀረበ በሚሆንበት ጊዜ ከሳሽ የስራ መሪ ሆነም አልሆነም ችሎቱ የዳኝነት ስልጣን የሚያጣበት የህግ መሰረት የለም፡፡ የፌደራል የስራ ክርክር ችሎቶች የተቋቋሙት በአዋጅ ቁጥር 25/1988 እንደመሆኑ የስልጣናቸው ወሰንም በስራ መሪ ጭምር የሚቀርብን ማናቸውንም የስራ ክርክሮች እንጂ ከአዋጅ ቁ 377/96 በሚመነጩት የስራ ክርክሮች የተገደበ አይደለም፡፡

ከሳሽ የስራ መሪ እንጂ ሰራተኛ አይደለም አቋም ከተያዘ በቀጣይነት የሚነሳው ጥያቄ ተፈጻሚ የሚሆነውን ህግ መለየት እንጂ የፍርድ ቤቱ ስልጣን አይደለም፡፡ ጉዳዩን የያዘው የፌደራል ፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎት ሆኖ በህግ እስከተቋቋመ ድረስ የስራ ክርክሩ መሰረት ያደረገበት ህግ የፍትሐ ብሄር የስራ ውል ድንጋጌዎች ሆነ አዋጅ ቁ 377/96 ሁለቱንም ያለ ልዩነት ተቀብሎ ዳኝነት ለመስጠት ከተቋቋመበት ህግ የመነጨ የዳኝነት ስልጣን አለው፡፡

ቸልተኝነት እና አስተዋዩ ውሻ

 ከውል ውጩ በሚደርስ ኃላፊነት ህግ ውስጥ የቸልተኝነት ጥያቄ ከተነሳ ምላሹ ለብዙ ፍርድ ቤቶች ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው፡፡ በብዙ የህግ ስርዐቶች ውስጥ ተቀባይነት ያገኘው የቸልተኝነት መለኪያ “የአንድ አስተዋይ ሰው ሚዛን” ሲሆን ይህም አንድ አስተዋይ ሰው በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆን ኖሮ ምን እንደሚያደርግ በመላምታዊ ፍሬ ነገር ላይ ተመስርቶ ማሰላሰልና ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡ እንግዲህ ቸልተኝነትን በአንድ አስተዋይ ሰው እይታ መዝኖ መወሰን አስቸጋሪ ከሆነ ይህን መለኪያ ለአንድ አስተዋይ ውሻ ተፈፃሚ ማድረግ ደግሞ በጣም ፈታኝ ብቻ ሳይሆን አስገራሚም ጭምር ነው፡፡

በአሜሪካም ኢሊዮኒስ ግዛት በኪርካም እና ዊል (Kirkham Vs. Will) መካከል በታየ አንድ የይግባኝ ክርክር ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በጉዳዩ የተነሳው ጭብጭ የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያ በመጠቀም እልባት ሰጥቶበታል፡፡ ክሱ የተጀመረው “የተከሳሽ ውሻ በንክሻ ላደረሰብኝ ጉዳት የውሻው ባለቤት የሆነው ተከሳሽ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል፡፡” በሚል ከሳሽ ባቀረበው ክስ ሲሆን ተከሳሹም በበኩሉ ከሳሽ የተነከሰው ውሻውን በመተናኮሉ ስለሆነ በራሱ ጥፋት ለደረሰበት ጉዳት ልጠየቅ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡ ክሱ በስር ፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ በኋላ በይግባኝ ክርክሩ ላይ በዋነኛነት የተነሳው ጭብጥ “መተናኮል አለ ወይስ የለም?” የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ ይህንን ጭብጥ ለመወሰን እንደመመዘኛ ወይም መስፈርት የተጠቀሙት የተለመደውን የአስተዋይ ሰው ሚዛን ሳይሆን የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያ ነበርር፡ በዚህ ሚዛን ወይም መለኪያ መሠረት መተናኮል አለ ወይስ የለም የሚለውን ጥያቄ ለመወሰን በተመሳሳይ ሄኔታዎች ውስጥ አንድ አስተዋይ ውሻ ተከሳሽ ካሳየው እንቅስቃሴ አንጻር ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል? የሚል መላምታዊ ጥያቄ አንስቶ ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተፈጻሚ ባደረግው መለኪያ መሰረት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

ከውል ውጩ በሚደርስ ኃላፊነት ህግ ውስጥ የቸልተኝነት ጥያቄ ከተነሳ ምላሹ ለብዙ ፍርድ ቤቶች ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው፡፡ በብዙ የህግ ስርዐቶች ውስጥ ተቀባይነት ያገኘው የቸልተኝነት መለኪያ “የአንድ አስተዋይ ሰው ሚዛን” ሲሆን ይህም አንድ አስተዋይ ሰው በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆን ኖሮ ምን እንደሚያደርግ በመላምታዊ ፍሬ ነገር ላይ ተመስርቶ ማሰላሰልና ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡ እንግዲህ ቸልተኝነትን በአንድ አስተዋይ ሰው እይታ መዝኖ መወሰን አስቸጋሪ ከሆነ ይህን መለኪያ ለአንድ አስተዋይ ውሻ ተፈፃሚ ማድረግ ደግሞ በጣም ፈታኝ ብቻ ሳይሆን አስገራሚም ጭምር ነው፡፡

በአሜሪካም ኢሊዮኒስ ግዛት በኪርካም እና ዊል (Kirkham Vs. Will) መካከል በታየ አንድ የይግባኝ ክርክር ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በጉዳዩ የተነሳው ጭብጭ የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያ በመጠቀም እልባት ሰጥቶበታል፡፡ ክሱ የተጀመረው “የተከሳሽ ውሻ በንክሻ ላደረሰብኝ ጉዳት የውሻው ባለቤት የሆነው ተከሳሽ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል፡፡” በሚል ከሳሽ ባቀረበው ክስ ሲሆን ተከሳሹም በበኩሉ ከሳሽ የተነከሰው ውሻውን በመተናኮሉ ስለሆነ በራሱ ጥፋት ለደረሰበት ጉዳት ልጠየቅ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡ ክሱ በስር ፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ በኋላ በይግባኝ ክርክሩ ላይ በዋነኛነት የተነሳው ጭብጥ “መተናኮል አለ ወይስ የለም?” የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ ይህንን ጭብጥ ለመወሰን እንደመመዘኛ ወይም መስፈርት የተጠቀሙት የተለመደውን የአስተዋይ ሰው ሚዛን ሳይሆን የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያ ነበርር፡ በዚህ ሚዛን ወይም መለኪያ መሠረት መተናኮል አለ ወይስ የለም የሚለውን ጥያቄ ለመወሰን በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ አንድ አስተዋይ ውሻ ተከሳሽ ካሳየው እንቅስቃሴ አንጻር ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል? የሚል መላምታዊ ጥያቄ አንስቶ ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተፈጻሚ ባደረግው መለኪያ መሰረት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

የስራ መሪ -የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ

የስራ መሪ የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ ክፍል አንድ

የስራ መሪ ትርጉም

ለስራ መሪ የተሰጠው ትርጓሜ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/1996 አንቀጽ 2(ሐ) ላይ የተመለከተ ሲሆን በሰበር በተሰጡ ውሳኔዎች የድንጋጌውን ይዘት እንደወረደ ከመድገም ባለፈ ድንጋጌውን ለመረዳት የሚያስችል ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም ትንተና አልተሰጠም ለምሳሌ በሰ.መ.ቁ. 42901 (አመልካች የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና ተጠሪ ወ/ሮ ንግሥት ለጥይበሉ ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም) በአንቀጽ 2(ሐ) ላይ የተመለከተው የስራ መሪ ትርጉም እንደወረደ ከመደገሙ በስተቀር በድንጋጌው ይዘት የታከለበት ማብራሪያ ሆነ ትንተና የለም

በአዋጁ አንቀጽ 2(ሐ) ላይ የስራ መሪ ትርጉም እንደሚከተለው ተቀምጧል
“የሥራ መሪ የሚባለው በሕግ ወይም እንደ ድርጅቱ የሥራ ፀባይ በአሠሪው በተሠጠው ውክልና ሥልጣን መሠረት የሥራ አመራር ፖሊሲዎችን የማውጣትና የማስፈፀም ከዚህ በተጨማሪ ወይም እነዚህኑ ሳይጨምር ሠራተኛን መቅጠር ማዛወር የማገድ የማሰናበት የመመደበ ወይም የሥነ ሥርዓት እርምጃ የመውሰድ ተግባሮችን የሚያከናውንና የሚወስን ግለሰብ ነው ፡፡”

ከዚህ ጠቅለል ካለው አገላለጽ በተጨማሪ ድንጋጌው የተወሰኑ ተግባራት የሚያከናውኑ ሰራተኞችን በስራ መሪነት ይፈርጃቸዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ከላይ የተመለከቱትን የስራ አመራር ጉዳዮች አስመልክቶ የአሰሪውን ጥቅም ለመጠበቅ አሰሪው ሊወስደው ስለሚገባው እርምጃ በራሱ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ባለሙያ የስራ ሐላፊም ጭምር እንደ ስራ መሪ ይቆጠራል፡፡
የስራ መሪ ትርጓሜ ላይ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 494/1998 ተሻሽሎ በአዲስ የተተካ ቢሆንም በይዘት ረገድ ግን የህግ አገልግሎት ሐላፊ እንደ ስራ መሪ በተጨማሪነት ከመካተቱ በቀር የተለወጠ ነገር የለም

የማስረዳት ግዴታ እና የማስረጃ ጫና

የስራ ክርክር ያቀረበ ሰራተኛ የስራ መሪ ነው የሚል መቃወሚያ በአሰሪው በኩል የተነሳበት እንደሆነ ይህንን የማስረዳት የማስረጃ ጫናው በአሰሪው ላይ ያርፋል ፡፡ (አመልካች ርሆቦት ሆሊሺየር ኃ/የተ/የግ/ማ እና ተጠሪ አቶ አማረ አድማሱ ሰ/መ/ቁ 38811 የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም)
ሰበር እዚህ ድምዳሜ ላይ ሊደርስ የቻለው የሰራተኛው የስራ ሀላፊነት የስራ መሪ የሚያደርገው ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በማስረጃ የሚረጋገጥ የፍሬ ነገር ጉዳይ ነው በሚል ምክንያት ነው፡፡ የሰበር ችሎት ተጠሪ የሥራ መሪ ናቸው በማለት አመልካች ያቀረበውን ቅሬታ ውድቅ ሲያደርግ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡
“የተጠሪ የስራ ሃላፊነት የስራ መሪ የሚያሠኛቸው ነው ወይስ አይደለም የሚለው በማስረጃ የሚረጋገጥ የፍሬ ነገር ጉዳይ እንደመሆኑ አመልካች ይህንኑ የማስረዳት ሸክም አለበት ነገር ግን ከመዝገቡ እንደተረዳነው በስር ፍ/ቤት አመልካች ይህንን ለማስረዳት ያቀረበው ማስረጃ የለም፡፡ በመሆኑም በዚህ በኩል ያቀረበው የሠበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፡፡”

ማስረዳት ስለሚቻልባቸው መንገዶች

የስራ መሪ ነው የሚል መቃወሚያ በአሰሪው በኩል ሲቀርብ ይህንኑ የማስረዳት ግዴታ የራሱ የአሰሪው ስለመሆኑ በሰ/መ/ቁ 38811 ላይ በሰበር አቋም የተወሰደበት ነጥብ ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣይነት የሚነሳው ጥያቄ አሰሪው ከሳሽ ሰራተኛ ሳይሆን የስራ መሪ እንደሆነ ማስረዳት የሚችልባቸው መንገዶች ምንድናቸው? የሚል ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ለሰበር ከቀረቡት ጉዳዮች ለመረዳት እንደሚቻለው በአሰሪው በኩል ሁለት የማስረጃ መንገዶች በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ሲሆን በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝተው ለሰበር ውሳኔዎች መሰረት በመሆን ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡እነሱም፡-

ሀ. የስራ ኃላፊነት መዘርዘር (ሰ/መ/ቁ 36894፤ 42901)
ለ. የህብረት ስምምነት (ሰ/መ/ቁ 39658፤ 38894፤ 42901)

ሀ. የስራ ኃላፊነት መዘርዘር

የስራ ኃላፊነት መዘርዝር ሰራተኛው በእርግጥ ሲሰራ የነበረው ስራ እና በእርግጥ የነበረው ስልጣን መሰረት የሚያደርግ ሳይሆን በድርጅቱ መዋቅር ለየመደብ ክፍሉ የስራ ኃላፊነት የተቀመጠ የስራ ተግባራት ዝርዝር ነው፡፡ ስለሆነም በወረቀት የተቀመጠውንና በተግባር ያለውን እውነታ የሚያስታርቅ አይደለም፡፡

በአመልካች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ አቶ ሙላት ታረቀኝ (የሰ.መ.ቁ. 36894 ታህሳስ 30 ቀን 2001 ዓ.ም) መካከል በነበረው ክርክር የሰበር ችሎት ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ በዋናነት መሰረት ያደረገው የተጠሪን የስራ ሃላፊነት ዝርዝር ነበር፡፡

ከሰበር ውሳኔው ለመረዳት እንደሚቻለው ተጠሪ ተመድበው ይሰሩበት የነበረው የሂሳብ ክፍል ረዳት ኃላፊ የሥራ ቦታ ላይ ሲሆን በቦታው ላይ የተመደቡትም በቋሚነት ሳይሆን በተጠባባቂነት (በአመልካች አገላለጽ ደግሞ በጊዜያዊነት) ነው፡፡ የሰበር ችሎት የተጠሪን የሥራ መደብ የሥራ መዘርዝርን በተመለከተ እንዳለው የተጠሪ የስራ ኃላፊነት የክፍሉን እንቅስቃሴዎች የመቆጣጠር፤ የዕለት ከዕለት የሒሳብ ቁልፎችን መያዝና የሒሳብ ከፋዮችን የዕለት ከዕለት የሥራ ምደባ ፕሮግራም ማዘጋጀትን ያጠቃልላል፡፡

ከዚሁ በመነሳት ተጠሪ የስራ ሃላፊነታቸው የስራ መሪ እንደሚያደርጋቸው የሰበር ችሎቱ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጉዳዩን በመጀመሪያ ያየው የፌደራል የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው በማለት በአመልካች የቀረበውን መቃወሚያ በመቀበል የተጠሪን የስራ ክርክር ክስ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ከዚህ ውሳኔ ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ የሻረው ሲሆን ለውሳኔው በዋናነት መሰረት ያደረገው ግን የሥራ መደቡ የሥራ መዘርዝር ተጠሪን የስራ መሪ አያደርጋቸውም በማለት ሳይሆን ተጠሪ ምክትል የግምጃ ቤት ሓላፊ በመሆን ያገለገሉት በጊዜአዊነት በመሆኑ በቋሚነት ተመድበው ያልሰሩበት የሥራ መደብ የሥራ መሪ ሊያሰኛቸው አይችልም የሚል ምክንያት በመስጠት ነው፡፡

የሰበር ችሎት የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሲሽር በመዝገቡ ላይ ከተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች አንጻር ፍርድ ቤቱ የፈጸመውን መሰረታዊ የህግ ግድፈት ከመመርመር አልፎ ያለስልጣኑ ተጨማሪ ፍሬ ነገሮችን አጣርቷል፡፡ ተጣርቷል የተባለው ፍሬ ነገር በሰበር ደረጃ ማስረጃ የቀረበበት ሳይሆን በችሎቱ ፊት የተደረገውን የቃል ክርክር መሰረት ያደረገ ነው፡፡

የሰበር ችሎት የተጠሪን የስራ መዘርዝር በማየት የስራ መሪ ናቸው ካለ በኋላ በቀጣይነት የመረመረው ጭብጥ ተጠሪ በሥራ መደቡ ይሰራ የነበረው በቋሚነት ሳይሆን በተጠባባቂነት መሆኑ ተጠሪን ሰራተኛ ያሰኘዋል ወይስ አያሰኘውም? የሚል ሲሆን ይህን ነጥብ በተመለከተም “ተጠሪ በተጠባባቂነት ተመድበው ሲሰሩ ለቦታው የሚገባውን ጥቅማጥቅም የሚያገኙ እንደነበርና ለሥራው ሙሉ ሃላፊነት ወስደው ይሰሩ እንደነበር” በስርና በሰበር ችሎቱ የተደረገው ክርክር እንደሚያሳይ ችሎቱ በውሳኔው ላይ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ ፍሬ ነገር በመነሳትም ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በሰበር በታየ ሌላ ክርክር (አመልካች የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና ተጠሪ ወ/ሮ ንግሥት ለጥይበሉ የሰ.መ.ቁ 42901 ሐምሌ 21 ቀን 2001 ዓ.ም.) ተጠሪ የድርጅቱ የሀገር ውስጥ ዕቃ ግዥ ዋና ክፍል ኃላፊ በመሆን እንዲሁም በተጨማሪነት የውጪ ሀገር ዕቃ ግዥ ዋና ክፍልና የሽያጭ ዋና ክፍልን የሚያካትተውን የንግድ መምሪያ ኃላፊነትን ደርበው ይሠሩ ነበር፡፡

የሰበር ችሎ በቀጣይነት የሥራ መደቡ ዋና ተግባራት ምንድናቸው? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ ጉዳዩን የመረመረ ሲሆን የተጠሪን የሥራ መዘርዝር /job description/ በመጥቀስ የሥራ መደቡ በአጠቃላይ በድርጅቱ መመሪያ መሠረት ማስተባበር፣ መምራት፣ ማደራጀት እና መቆጣጣር እንዲሁም ዕቅድና በጀት ዝግጅት ላይ መሳተፍ እንደሚያጠቃልል በውሳኔው ላይ አመልክቷል፡፡

በመቀጠለም “ተጠሪ ሥራን የማቀድ፣ የመምራት፣ የመቆጣጠር፣ የማደራጀትና የማስተባበር ተግባራትን የሚያከናውኑ መሆኑን ከክርክሩም ሆነ ከቀረቡ ሰነዶች መረዳት” እንደተቻለ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
ከዚህ በመነሳትም “የተጠሪ የሥራ ተግባር በፍሬ ነገር ረገድ የተረጋገጠው የድርጅቱን ዋና ክፍል ሥራ በኃላፊነት መምራት፣ ማደራጀት መቆጣጠርና ማስተባበር ከመሆኑ አንፃር በሕጉ ትርጉም ከተሠጠው የሥራ ዘርፍ የሚመደቡ በመሆናቸው የሥራ መሪ ናቸው እንጅ ሠራተኛ አይደሉም፡፡” የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ተጠሪ የስራ መሪ አለመሆናቸውን ለማሳየት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቦርድም የማናጅመንት አባላት ክፍያ አፈፃፀም መመሪያ እሳቸውን እንደማይሸፍን በመጥቀስ የማናጅመንት አባል አለመሆናቸው ሰራተኛ እንደሚያደርጋቸው ለችሎቱ ክርክራቸውን ያቀረቡ ሲሆን ችሎቱም በማናጅመንት አባልና በስራ መሪ መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ሳያመለክት ክርክራቸውን ለጉዳዩ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎባቸዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ ሰበር ትንተና የሰጠው በሚከተለው መልኩ ነበር፡፡

“የመንግስት የልማት ድርጅቶች የቦርድም የማናጅመንት አባላት ክፍያ አፈፃፀም መመሪያ እኔን አይጨምርም በማለት ከተጠሪ የቀረበውን ክርክር በተመለከተ መመሪያው ለቦርድና ማናጅመንት አባላት ሊከፈል የሚገባውን ክፍያ አስመልክቶ የወጣ የአፈፃፀም መመሪያ እንጅ ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚ ስለማይሆን ለክርክሩ አግባብነት የሌለው ነው፡፡”

ለ. የህብረት ስምምነት

የህብረት ስምምነት በአሰሪ በኩል የስራ መሪን ለማስረዳት የሚቀርብ ሌላው የማስረጃ መንገደ ሲሆን በሰበር በኩልም ያለአንዳች ትችት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

በሰ.መ.ቁ.36894 እና ሰ.መ.ቁ.42901 በሰበር በተሱጡት ውሳኔዎች ላይ ምንም እንኳን የስራ ኃላፊነት መዘርዝር የስራ መሪን ለማስረዳት በሰበር በኩል ተቀባ ይነት ቢያገኝም ብቻውን የቆመ ምክንያት ግን አልነበረውም፡፡ በሁለቱም መዝገቦች ላይ የሰራተኛው የስራ መዘርዘር ከተጠቀሰና ከተለየ በኃላ ‘የስራ መሪ ነው’ የሚል መደምደሚያ ላይ ሲደረስ የኅብረት ስምምነትም እንደማጠናከሪያነት ተጠቅሷል ስለሆነም በሁለቱም መዝገቦች የስራ መዘርዝር ባልቀረበበት ሁኔታ አንድ የስራ ክፍል በህብረት ስምምነት በስራ መሪነት ስለተፈረጀ ብቻ በዚያ የስራ ክፍል ላይ ተመድቦ የሚሰራ ግለሰብ እንደ ስራ መሪ አልተቆጠረም፡፡

ሰራተኛው የሕብረት ስምምነቱ ሰራተኛ ሳይሆን የስራ መሪ የሚያደርገው ቢሆንም የሰበር ችሎት በሰ.መ.ቁ.36894 እና ሰ.መ.ቁ.42901 ለውሳኔው በዋናነት መሰረት ያደረገው ግን የስራ መዘርዘሩን ነው፡፡
ይሁን እንጂ በአመልካች የሸዋ ጥጥ ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ተጠሪ አቶ ታከለ ቀፀላ (የሰ.መ.ቁ 39658 ሐምሌ 23 ቀን 2001 ዓ.ም) መካከል በነበረው ክርክር ምንም አይነት የስራ መዘርዘር ሳይቀርብ የስራ መደቡ በህብረት ስምምነት ላይ መጠቀሱን መሰረት በማድረግ ብቻ ተጠሪ የስራ መሪ ናቸው የሚል ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ከውሳኔው ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት ክስ ሲያቀርቡ የፈረቃ ምርት ሀላፊ መሆናቸውን በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ የሰበር ችሎቱ ከዚህ በመነሳት “ተጠሪ በክሳቸው የገለፁት እና የተመደቡበት የኃላፊነት ቦታ በአመልካችና በአመልካች ድርጅት ያሉ ሠራተኞች ባቋቋሙት የሠራተኛ ማህበር ድርድር ባፀደቀው ሶስተኛው የህብረት ስምምነት በአንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 6 /ሐ/ የሥራ መሪ መሆናቸው” በግልፅ እንደተደነገገ በመጠቆም የህብረት ስምምነቱን ይዘት ምን እንደሆነ በውሳኔው ላይ ሳያሰፍር ተጠሪ የሥራ መሪ ናቸው የሚል አቋም ላይ ደርሷል፡፡

የስር ፍርድ ቤቶች የሰጧቸውን ውሳኔዎችንም እንደሚከተለው ተችቷል፡፡
“ተጠሪ የሥራ መሪ መሆናቸው አመልካችና የሠራተኛ ማህበሩ ባደረጉት ድርድር በፀደቀው ሶስተኛው የሕብረት ስምምነት በግልፅ በተደነገገበት ሁኔታ የበታች ፍርድ ቤቶች ህብረት ስምምነቱን ድንጋጌ ወደ ጎን በመተው ተጠሪ ሠራተኛ ነው በማለት የደረሱበት መደምደሚያና ለተጠሪ ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የሰጡት ውሣኔ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 3/2/ሐ እንደተሻሻለ የሚተላለፍ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡”
አንድ ተቀጣሪ የስራ መሪ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጥያቄ በበአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 3/2/ሐ እንደተሻሻለ በተቀመጠው መለኪያ ተመዝኖ በፍርድ ቤቶች ፍርድ ማግኘት ያለበት ነጥብ እንጂ ሰራተኛውና አሰሪው ተደራድረው በህብረት ስምምነት የሚወስኑት የስራ ሁኔታ ስላለመሆኑ ከድንጋጌው ምንባብ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግት አይደለም፡፡ የሰበር ችሎት ይህን ነጥብ መዘንጋቱ የተሳሳተ ውሳኔ እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡

በተጨማሪም የህብረት ስምምነት ከተዋዋይ ወገኖች በዘለለ በድርድሩ ላይ ምንም ተጽዕኖ ሆነ ሚና ባልነበራቸው ግለሰቦች ላይ እንዴት ተፈጻሚነት ሊያገኝ እንደቻለ ሌላው በሰበር ያልተመለሰ ጥያቄ ነው ችሎቱ ጥያቄውን መጀመሪያውኑ ባለማንሳቱ ውሳኔውም የተሳሳተ ሊሆን ችሏል፡፡

በአንድ ውሳኔ ሁለት ጊዜ የፍርድ ባለዕዳ! (የሰበር መ.ቁ. 19205)

(ውሳኔውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ፡፡)

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡  በፍርድ ቤት የተወሰነበትን ገንዘብ በአፈጻጸም እንዲከፍል አቤቱታ የቀረበበት የፍርድ ባለዕዳ እንደፍርዱ ሊፈጽም ባለመቻሉ ቤቱ ተሽጦ ለዕዳው መክፈያነት እንዲውል አፈጻጸሙን የሚያየው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ሆኖም በትዕዛዙ መሰረት ቤቱ ከመሸጡ በፊት የፍርድ ባለዕዳው የሚፈለግበትን 20,000 ብር (ብር ሃያ ሺ) በሞዴል 85 ያስይዛል፡፡ በመቀጠል የፍርድ ባለመብቱ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ እንዲለቀቅለት ለፍርድ ቤቱ አመለከተ፡፡

ገንዘብ በሞዴል 85 ከተያዘ በኋላ አፈጻጸም ቀላልና ያለቀለት ጉዳይ ቢሆንም የፍርድ ባለመብት ባቀረበው አቤቱታ መሰረት የተያዘውን ገንዘብ ማግኘት አልቻለም፡፡ ምን ተፈጠረ? መጀመሪያ አፈጻጸም የተከፈተበት መዝገብ ጠፋ ተባለ፡፡ ተባለ  ብቻ ሳይሆን በቃ ጠፋ! በመዝገብ መጥፋት የትኛውም ፍርድ ቤት ቢሆን ስሙ መነሳት ባይኖርበትም መልካም የፍርድ ቤት አስተዳደር ባለበት ፍርድ ቤት ውስጥ እንኳን ሳይቀር የመዝገብ መጥፋት አንዳንዴ ይከሰታል፡፡ ደግነቱ የጠፋው መዝገብ የአፈጻጸም በመሆኑ ሌላ የአፈጻጸም መዝገብ መክፈት የሚቻል በመሆኑ በፍርድ ባለመብት ላይ ከሚያስከትለው አላስፈላጊ ወጪና መጉላላት በቀር የከፋና የማይመለስ ጉዳት የማድረስ ውጤት የለውም፡፡ እናም በዚህኛው በጠፋው የአፈጻጸም መዝገብ ምትክ በፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ትዕዛዝ ሌላ የአፈጻጸም መዝገብ እንዲከፈት ተደረገ፡፡

ሆኖም ነገሩ በዚህ አላበቃም፡፡ የመዝገቡ መጥፋት ሳያንስ ሌላ ጉድ የሚያሰኝ ነገር ተከሰተ፡፡ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ ጠፋ!! አዲስ በተከፈተው መዝገብ ላይ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ገንዛብ ወጪ ሆኖ ለፍርድ ባለመብት እንዲከፈል ትዕዛዝ ሲሰጥ ትዕዛዙ የደረሰው የፋይናንስ ቢሮ በሞዴል 85 ተይዞ የነበረው ገንዘብ ፍርድ ቤቱ ራሱ  በ5/5/89 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ገንዘቡ አቶ ኤልያስ አርአያ ለተባለ ግለሰብ መከፈሉን በመግለፁ ነገሩ ሁሉ ፍጥጥ ፍጥጥ ሆነ፡፡

እንግዲህ ያለው መፍትሄ ምንድነው? በአንድ በኩል የፍርድ ባለመብት መብቱን በህግ ሀይል ለማስከበር ክስ አቅርቦ ተከራክሮ አሸንፎ ተፈርዶለት የፍርዱን ፍሬ በአፈጻጸም እንዲከፈለው ከችሎቱ ፊት ቆሟል በሌላ በኩል የፍርድ ባለዕዳው መጀመሪያ በቀረበበት ክስ  በመረታቱ እንደ ፍርዱ ፈጽም ሲባል የሚፈለግበትን ገንዘብ በተለመደው ህጋዊ ስነ ስርዓት መሰረት ‘አድርግ!’ እንደተባለው ገንዘቡን በሞዴል 85 ገቢ አድርጓል የፍርድ ባለዕዳ ሆነ የፍርድ ባለገንዘብ በዚህ መዝገብ ላይ በተፈጠረው አሳዛኝ አጋጣሚ ስህተትም ሆነ ጥፋት የለባቸውም ጥፋቱ ግራ ቀኙን  አይቶ ፍትህ በሚያጎናጽፈውና ዳኝነት በሚሰጠው በራሱ በፍርድ ቤቱ እንደሆነ ግልጽ ነው

በአጠቃላይ በመጨረሻ  ወደ ሰበር ያመራው ጉዳይ አመጣጥና የታሪኩ መነሻ ከላይ የተገለጸው ሲሆን የተፈጠረው ክስተት ጉዳዩን ትኩረት የሚስብ አድርጎታል፡፡  የበለጠ ትኩረትን የሚስበው ግን ክስተቱ ሳይሆን ለክስተቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ  በየደረጃው ጉዳዩ የቀረበላቸው ፍርድ ቤቶች መፍትሄ ይሆናል በሚል የሰጡት ትዕዛዝ እና ውሳኔ ነው፡፡

በመጀመሪያ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ ለሌላ ሰው መከፈሉን ያወቀው አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤት “የፍርድ ባለዕዳ ገንዘቡን በፍርደ ቤት ካስያዘ በፍርድ ቤት እንደተቀመጠ ስለሚቆጠር የፍርድ ባለመብት ጉዳዩን ተከታትሎ ገንዘቡ ለሌላ 3ኛ ወገን እንዲከፈል ምክንያት የሆነውን አካል ጠይቆ ገንዘቡን ከሚቀበል በቀር ከፍርድ ባለዕዳ ድጋሚ መጠየቅ አይችልም” በማለት ወሰነ ይህ ውሳኔ በይግባኝ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሻረ ሲሆን የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ የጠቅላይ ፍርድ ቤት መልሶ ሽሮታል፡፡ ፍርድ ቤቱ  ውሳኔውን ሲሽር የሰጠው ምክንያት “የፍርድ ባለዕዳ በሞዴል 85 ያስያዘውን ገንዘብ በፍትሃብሄር ስነ ስርዓት ህግ ቁ. 395 መሰረት እንደተከፈል ይቆጠራል” የሚል ሲሆን በይዘቱ አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤት ከሰጠው ውሳኔ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ በመጨረሻ ጉዳዩ ሰበር ደረሰ፡፡ የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክርና የስር ፍርደ ቤቶችን ውሳኔዎች ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን ጭብጥ በመያዝ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ሰበር ችሎቱ ምላሽ ያሻዋል በሚል የያዘው ጭብጥ “በሞዴል 85 ተይዞ የነበረው ገንዘብ ለሌላ 3ኛ ወገን ቢከፈልም ለአሁን አመልካች እንደተከፈለ መቆጠሩ አግባብ ነው ወይስ አይደለም?”  የሚል ነው፡፡

ችሎቱ ለተያዘው ጭብጥ ምላሽ ለመስጠት የራሱን ትንተና ከሰጠ በኋላ በመጨረሻ ላይ የደረሰበት ድምዳሜ የሚከተለው ነበር፡፡

“በፍርድ ቤት ገንዘብ ገቢ በማድረግ እዳ መክፈል አንድ አማራጭ መንገድ ቢሆንም የፍርድ ባለእዳው እዳውን ጨርሷል መባል ያለበት ይህ ሂደት ተጠናቆ የፍርድ ባለመብቱ ገንዘቡን ሲረከብ ሊሆን ይገባል፡፡

ሰበር ችሎቱ ይህን አቋሙን ሲያጠናክር በተጨማሪነት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

“የፍርድ ባለመብቱ ገንዘቡን ባልተረከበበት ሁኔታ የፍርድ ባለዕዳው እንደከፈለ መቁጠሩ አግባብ አይደለም፡፡ የፍርድ ባለዕዳው ያስያዘው ገንዘብ ፍርዱ ከመፈጸመ በፊት ተመልሶ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተከፈለ ባለዕዳው ገንዘብ እንዳስያዘ ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ያስያዘው ገንዘብ ሳይኖር በፍትሃብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 395(2) መሰረት ፍርዱ እንደተፈጸመ ሊቆጠር አይገባውም፡፡

በዚሁ መሰረት የሰበር ችሎቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማጽናት የፍርድ ባለዕዳው ለብር 20,000 (ሃያ ሺ ብር) ተጠያቂ ነው የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ለመሆኑ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ እንዴት ሊከፈል ቻለ? የተከፈለውስ ለማን ነው?

ለዚህ ጥያቄ በሰበር ችሎቱ ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ ሰበር ችሎቱ በዚህ ረገድ በውሳኔው ላይ እንዳሰፈረው በሞዴል 85 ተይዞ የነበረውን ገንዘብ ወሰደ የተባለው ግለሰብ በምን ምክንያት እንደወሰደ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ገንዘቡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደተለቀቀለት ችሎቱ ከፍርድ ቤቶቹ መዝገብ እንደተረዳ ሳየጠቁም አላለፈም፡፡

በዚህ መልኩ የተገለጸውና ያልተገለጸው ከተለየ በኋላ ከሁለቱ ውጪ የሆነ ሌላ ፍሬ ነገር ደግሞ በራሱ በችሎቱ ታከለበት እንዲህ የሚል፡፡

“…ይህ ገንዘብ ለአሁን መልስ ሰጪ እዳ መክፈያ ውሎ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል”

ግምት ነው እንግዲህ!

ሲጠቃለል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ፤ በፍርድ ቤት ስህተት፤ በፍርድ ቤት ጥፋት ለተከፈለው ገንዘብ ተጠያቂ ነህ የተባለው ፍርድ ቤቱ ሳይሆን የፍርድ ባለዕዳው ነው፡፡